የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው  ሲሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ። 

በገበታ ለአገርና በገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማትና ከተማን ማስዋብ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ውብና አዲስ ገጽታን ከማላበስ ባለፈ የዜጎችን በምቹና ንጹህ አካባቢ የመኖር መብት ያስከበረ ለመሆኑ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። 

ከተማዋ ከሌሎች አለምአቀፍ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆንና የአፍሪካ መዲናነቷን አስጠብቃ ለማቆየትም የኮሪደር ልማቱ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የአፋርና፣ኦሮሚያ ክልሎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማትን አድንቀዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንተነህ አዲሱ ፕሮጀክቶቹ የወንዝ ተፋሰሶችን፣ የብስክሌትና እግረኛ መንገዶችን ያቀፉ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

የአፋር ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዳኦድ አሞሎ፣የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነትን ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።


 

ቀደም ሲል በከተማ ማስዋብ ፕሮጀክት ተሳታፊ እንደነበሩም ነው ያስታወሱት።

የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባል ሽቶ ጀማል በበኩላቸው አዲስ አበባ በየዓመቱ የተለያዩ ለውጦችን እያሳየች ነው ብለዋል።


 

ልማቱ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን መቻሉ የአመራሩን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑንም አንስተዋል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ  በጉልበት ፣ በዕውቀትና በገንዘብ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አካባቢን ውብና ጽዱ ማድረግ የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑንና ኢትዮጵያን የሚመጥን ልማት በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።  

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ (7 ኪ.ሜትር) ፣ ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ (4.9 ኪ.ሜትር) ናቸው።

እንዲሁም ከመገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል የዓድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ (6.4 ኪ.ሜትር) እና ከፒያሳ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ በለገሃር ሜክሲኮ፣ በሳር ቤት በኩል እስከ ወሎ ሰፈር (10 ኪ.ሜትር) ናቸው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም