ተቋማቱ በችግኝ እንክብካቤ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ በችግኝ እንክብካቤ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ ፤ ሃምሌ 12/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌኮም እና ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በችግኝ እንክብካቤ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምድራችን ሁለንተናዊ ቀውስ ይዞ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም አንዱ አማራጭ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የተራቆቱ አካባቢዎችን የመመለስ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
በሐምሌ 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መልከ ብዙ ትሩፋቶች ይዞ መጥቷል።
ትውልዱ ዛሬ አሻራውን በማኖር አረንጓዴ ገጽታን ለተተኪ ትውልድ ለማውረስ ውጥን በያዘው በዚህ መርሐ ግብር አማካኝነት ባለፉት አምስት ዓመታት ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተክሏል።
በዚህ ሂደት የተለያዩ ግለሰቦች፣ ማህበራት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በየፊናቸው አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።
በርካቶቹ ከመትከል ባሻገር የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ትውልድ ዘለል ፋይዳ የሰነቀው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ካስገኛቸው ተጓዳኝ ትሩፋቶች መካከል አንዱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ ነው።
በዚህ ረገድ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በስፋት ከሚሳተፉና በችግኝ እንክብካቤ ሰፊ የስራ ዕድል ከፈጠሩ ተቋማት መካከል የኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ይገኙበታል።
በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት የሚሳተፈው ኢትዮ ቴሌኮም 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ገደማ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሽ ነው።
ኩባንያው በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ ተገቢውን እንክብካቤ እያከናወነ ሲሆን ለዚህ ይረዳው ዘንድ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን በመቅጠር ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን አዲስ አበባ ዞን የፍሪ ቶፕ ሱፐርቫይዘር አቶ ገረመው ጫልቃ እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት በዞኑ ብቻ ከ25 ሺህ በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የጽድቀት መጠናቸውም 80 በመቶ ደርሷል።
በየዲስትሪክቶች የተተከሉ ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ ቋሚ እንክብካቤ የሚያደርጉ ማህበራት ተደራጅተው የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገላችው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ ተከላ ባለፈ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር አካባቢ የጥራት ማረጋገጥ ክፍል ኃላፊ አቶ ታደለ ደገፋ በችግኝ ተከላ አሻራን ማኖር ብቻ ሳይሆን ችግኙን መንከባከብ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው ይላሉ።
ባለፉት ዓመታት የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች በየዓመቱ የምግብን ዋስትና ሊያረጋግጡ የሚችሉትን ጨምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች መትከላቸውን ያወሳሉ።
ተቋሙ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ችግኞች ከታለመላቸው ደረጃ እንዲደረሱ ፅድቀታቸውንና ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ 300 ቋሚ ሰራተኞችን በመቅጠር እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በችግኝ እንክብካቤ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካካል አቶ ጌጤነህ ዓለሙ እና አቶ አበበ ጌታቸው ለሕይወት መሰረት የሆኑ ዕጽዋትን በመንከባከባቸውና በመጠበቃቸው ትልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ ከሚያተርፈው በረከት ባሻገር ለእነርሱ እና መሰሎቻቸው የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ምክንያት ስለመሆኑ ይመሰክራሉ።
በየዓመቱ በንቅናቄ የሚተከሉ ችግኞች ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል የሚሉት ወጣቶቹ፣ በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ችግኞችን ከመንከባከብ ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ይገልጻሉ።