ቀጥታ፡

የተደራጀ መረጃን በፍጥነት የሚያደርሱ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጅ መረጃ መሰብሰቢያ አውታሮችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ):- የተደራጀ መረጃን በፍጥነት የሚያደርሱ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጅ መረጃ መሰብሰቢያ የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ እያከናወነ  መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

በተ.መ.ድ የልማት ፕሮግራም ድጋፍ በትግበራ ላይ በሚገኘው ''የቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም'' ኢኒሼቲቭ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በኢኒሼቲቩ ከታቀፉ 13 የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በመድረኩ ላይ የእስከዛሬ ተሞክሮዋን አቅርባለች።

ውይይቱ በኢኒሼቲቩ ዕቅድ፣ ትግበራ እና ለቀጣይ ግብዓት በሚሆኑ አበይት ጉዳዮች ላይ መምከሩን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይም ዕውቀት መር መረጃ አሰባሰብ፣ የአየር ትንብያ ስርዓት ምልከታዎችን የማጠናከር እና በመረጃ ተደራሽነት ዙሪያ በዝርዝር መምከሩን ተናግረዋል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ ምርትና ምርታማነት እንዲሰፋ ዕድል እንደሚፈጥር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን በማደራጀት የአደጋ ስጋትን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልጸው፤ ይህም ለተቋሙ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በፍጥነት እና በተደራጀ መልኩ መረጃ የሚያደርሱ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጅ መረጃ መሰብሰቢያ የመሰረተ ልማት አውታሮችን የማስፋት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያረጋገጡት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም