ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል-ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል-ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 11/2016(ኢዜአ)-ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ነጋዴው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽ እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዳውድ ሃመሎ ቀደም ሲል ነጋዴው ሲያነሳቸው የነበሩ የመብት ጥያቄዎች ጭምር ተቀባይነት እንዳልነበራቸው አስታውሰዋል።
በየደረጃው ያሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችም የነበራቸው ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ አልነበሩም ብለዋል።
ይሁንና ከአገራዊ ለውጡ በኋላ መንግስት ነጋዴው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ህጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንተነህ አዲሱ በበኩላቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ነጋዴውንና መንግስትን የሚያገናኙ ድልድዮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ምክር ቤቶቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መንግስት እየሰጠው ያለው ምላሽ የሚያበረታታ መሆኑን በማንሳት።
ፕሬዝዳንቶቹ አክለውም ነጋዴው በተለይም ህብረተሰቡን እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት በማረጋጋትና የስራ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል የተጣለበትን ሃላፊነት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፣ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች የተቋቋሙበትን ዕድሜ ያህል ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የምክር ቤቶች ጠንካራ ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን መደገፍና የአባላቱን ቁጥር ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
ከአገራዊ ለውጡ በኃላ የንግድ ህጉ መሻሻል፣ የካፒታል ገበያ መቋቋምና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎች በመወሰዳቸው ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ህጎችና ፖሊሲዎችን በአግባቡ ተረድቶ ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ መስጠት የሚችል ዕውቀት መር የሆነ አመራር ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነጋዴዎች ቢኖሩም የተደራጀና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የሚፈለገው ውጤት አልመጣም ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከትና የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል።
ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ የሚወዳደሩት ሰብስብ አባፍራ ከኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ አሰፋ አላምረው ከአማራ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንዲሁም መሰንበት ሸንቁጤ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ናቸው።