የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት የሚያስችል ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት የሚያስችል ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ11/ 2016 (ኢዜአ)፡- የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት የሚያስችል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የክልሉ መንግሥት በሱሉልታ ከተማ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመርቋል።
ፕሮጀክቱን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ-ልማትን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የስኬት ተምሳሌት በሆነችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ስም ተገንብቶ የተመረቀው ኢንስቲትዩትም የዚሁ ሥራ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ዓመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ በተለያዩ ችግሮች ሳይጠናቀቅ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ለስፖርቱ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ ስፖርቱን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
በአንድ ጊዜ በ16 የስፖርት አይነቶች 800 ስፖርተኞችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩቱ ብቁ አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች።
ለሀገር ላበረከተችው አስተዋጽዖ እውቅና በመስጠት ኢንስቲትዩቱ በስሟ በመሰየሙ የላቀ ምስጋናዋን አቅርባለች።
“ኢንስቲትዩቱ ከሰራሁት በላይ ታሪክ ያለው ለወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፤ ዜጎች ለሀገራቸው በቻሉት አቅም ሊያገለግሉ ይገባል” በማለትም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
በክልሉ ከዚህ በፊት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ካሉት መካከል የአምቦ ጎል (ፊፋ) እግር ኳስ አካዳሚ፣ የቦቆጂ እና ቦሬ አትሌቲክስ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ይገኙበታል፡፡