አዲሱን የመኖሪያ ቤት የአከራይ ተከራይ አዋጅ በሐዋሳ ከተማ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱን የመኖሪያ ቤት የአከራይ ተከራይ አዋጅ በሐዋሳ ከተማ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 11/ 2016 (ኢዜአ)፡- አዲሱን የመኖሪያ ቤት የአከራይ ተከራይ አዋጅ በሐዋሳ ከተማ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምከትል ኃላፊ አቶ አማዶ ኡዴሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሐዋሳ ከተማ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው አዋጅ በክልሉ ከተሞች እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ ተፈጻሚ ይሆናል።
የአዋጁን አተገባበር ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በሐዋሳ ከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ ለሚገኙ አመራር አባላት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ የመኖሪያ ቤቶች የአከራይ ተከራይ አዋጅ መሠረት በማድረግ ምዝገባና ውል እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በክልሉ የማስፈጸሚያ መመሪያና የህግ ማእቀፍ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ " የአከራይና ተከራይ ምዝገባና ውል የማፈራረሙን ስራ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
የቢሮው ምከትል ኃላፊ አክለው አዲሱ አዋጅ አከራዩንም ሆነ ተከራዩን ተጠቃሚ የሚያደርግና ሚዛን የሚያስጠብቅ እንዲሁም የቤት ኪራይ ዋጋ የሚተምኑት አከራይና ተከራይ ብቻ መሆናቸውም ፍትሀዊነት እንደሚያረጋግጥ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመፍታት ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን ለማየት የሚረዱ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት መቀረጹንም ተናግረዋል።
በዚህም እሰካሁን በክልሉ በሪል ስቴት የተሰማሩ ሶስት ድርጅቶችን ጨምሮ በማህበር ለተደራጁ ቤት ሰሪዎችም በየደረጃው የቤት መስሪያ ቦታና ብድር እየተመቻቸ እንደሚገኝ አውስተዋል።
በሐዋሳ ከተማ የመሀል ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ አበራ ደገፉ በክፍለ ከተማው በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች አከራይና ተከራዮችን ውል እያስፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለተግባራዊነቱ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ መቋቋሙንና በየደረጃው ለሚገኙ አመራር አባላትና ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ስራው በተሳለጠ መንገድ እየሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሐዋሳ ከተማ የአዲስ አበባ ቀበሌ ነዋሪና የመኖሪያ ቤት አከራይ አቶ አንተነህ አበበ "አዋጁ የአከራይና ተከራይ መሰረታዊ መብቶችን የሚያረጋግጥና ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ጠቀሜታው ብዙ ነው" ብለዋል።
"በተለይ አዋጅ የቤታችንን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ውል መቋረጥን በማስቀረት አስተሳስሮ ያኖረናል" ሲሉም ተናግረዋል።
በክፍለ ከተማው የለኩ ቀበሌ ነዋሪና ተከራይ ወይዘሮ ዘነበች ዘካሪያስ፤ የቤት ኪራይ ጉዳይ ለዓመታት ዋና ችግር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም አዋጁ ተገቢ ያልሆነ የኪራይ ዋጋ ጭማሬን ለማስቀረት፣ አከራዩንም ሆነ ተከራዩን በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግና አለመግባባቶችን የሚፈታ እንደሆነ አመልክተዋል።
አዲሱ የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ አዋጅን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል።