የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፌደራል ፖሊስ አቪዬሽን ፖሊስ መምሪያ የገነባው መኖሪያ ካምፕ ተመርቆ አገለግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፌደራል ፖሊስ አቪዬሽን ፖሊስ መምሪያ የገነባው መኖሪያ ካምፕ ተመርቆ አገለግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/ 2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ76 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አቪዬሽን ፖሊስ መምሪያ የገነባው የመኖሪያ ካምፕ ተመረቆ አገለግሎት መስጠት ጀመረ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አየር መንገድ መመኪያችን፣ የአንድነታችን ምልክትና ተምሳሌት የሆነ ታሪካዊና አንጋፋ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
በአየር መንገዱ ረጅም ታሪክ ውስጥ እና ድርጅቱ አሁን ላይ ለደረሰበት ስኬት የፖሊስ ድርሻ በደኅንነት ሥራው የላቀ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሴኩሪቲ ሴክተር ሪፎርም መሠረት የአቪዬሽን ፖሊስ መምሪያን በአዲስ መልክ አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱንና ለአመራርና አባላት ስልጠናዎችን በመስጠት በአዲስ አበባና በክልሎች ለሚገኙ አየር መንገዶች ደረጃውን የጠበቀ የፀጥታና ደህንነት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኩረት ሰጥቶ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን አጠቃላይ አገልግሎቱን ማሳደግ የሚያስችሉ አቅሞችን በመፍጠር እየሰራ መሆኑንና በዛሬው ዕለት የተመረቀው የፖሊስ መኖሪያ ካምፕ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ ከዚህ በፊት ላከናወናቸውና በቀጣይም በክልል አየር መንገዶች ለሚሰራቸው የሠራዊቱ መኖሪያ ካምፖች ለሚያደርገው እገዛ ኮሚሽነር ጀነራሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የአትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው፣ ለአየር መንገዱና ለመንገደኞች ሰላምና ደኅንነት ዘብ ነው ብለዋል።
አያይዘውም አየር መንገዱ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ አየር መንገድ በመባል ላስመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተሳትፎ ከፍተኛና የአየር መንገዱ ደጀን መሆኑን ተናግረዋል።