አሽከርካሪዎችና እግረኞች በኮሪደር ልማት የተገነቡ መንገዶችን ህግ አክብረው ሊጠቀሙ ይገባል-የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦ አሽከርካሪዎችና እግረኞች በኮሪደር ልማት የተገነቡ መንገዶችን ህግ አክብረው ሊጠቀሙ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጀመንት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ባለስልጣኑ የኮሪደር መንገድ አጠቃቀምና በክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበዉ ሚደቅሳ እንደተናገሩት፤ እግረኞች፣ አሽከርካሪዎችና ብስክሌተኞች የመንገድ ትራፊክ ደንብን በአግባቡ እንዲገነዘቡ እየተሰራ ነው።

በመዲናዋ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከግንዛቤ ባሻገርም የትራንስፖርት ደንብ ጥሰት በሚፈፅሙት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ እግረኞች ከዝናብ ለማምለጥ በፍጥነት መንገድ በሚያቋርጡበት ጊዜ ሊያጋጥም ከሚችል የትራፊክ አደጋ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

አሽከርካሪዎችም ፍጥነት በመቀነስና ለእግረኞች ቅድሚያ  በመስጠት እንዲያሽከረክሩም ጠቁመዋል።


 

በሌላ በኩል በመዲናዋ በኮሪደር ልማት ለአሽከርካሪዎች፣ እግረኞች አካል ጉዳተኞችና ብስክሌተኞች የተለዩ ራሳቸውን የቻሉ መንገዶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

መንገዶቹ ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም የጠየቁት አቶ ክበበው፥ ከዚህ አኳያ ህግ አክብሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸዉ ተርሚናል ውጭ ተሳፋሪ ማዉረድ፣ መጫንና መኪና ማቆም የተከለከለ መሆኑን ማወቅ አለባቸው  ብለዋል፡፡

 

በኮሪደር መንገዱ ላይ ከተፈቀደለት መስመር ውጭ የሚንቀሳቀስ አሽከርካሪም ሆነ እግረኛ ለቅጣት እንደሚዳረግና ይህንን ለመደንገግም ህግ መውጣቱን አብራርተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የትራፊክ ፖሊስ አባላት፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ህግ አስከባሪዎች፣ ብስክሌተኞችና ሌሎችም የትራንስፖርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም