ቀጥታ፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝወውርን ለመከላከልና አጥፊዎች የህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ፍትህ ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦ህገ ወጥ የሰዎች ዝወውርን ለመከላከልና ወንጀለኞችን የህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው በሰው የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ማሻገር ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ህገ ወጥ የፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያ መሆኗን አመልክተዋል፡፡

ይህንንም ችግር ታሳቢ ባደረገ መልኩ እስከ ወረዳ የሚወርድ መዋቅር በመዘርጋት በሰዎች መነገድና ህገ-ወጥ ስደትን የመከላከል ቅንጅታዊ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከ32 የመንግስት ተቋማትና ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በትብብር ጥምረቱ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት፣ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም፣ የወንጀል መከላከልና የህግ ማስከበር፣ የጥናትና ምርምር፣ የመረጃ አስተዳደር፣ እና የዲያስፖራ ተሳትፎ የስራ ቡድን በማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ በወንጀል መከላከልና በህግ ማስከበር ስራ በ130 መዝገቦች በቀጥታ ክስ የተመሰረተ ሲሆን በስምንት መዝገቦች ላይ እስከ አምስት አመት የሚደርስ የፍርድ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል።

ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ መዝገቦች በየዓመቱ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ እያሳዩ በመምጣታቸው የትብብር ጥምረት አባል ተቋማት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል። 

በቅርቡም ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ የታገዝ ነጸ የስልክ ጥሪ ማዕከል "6073" አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህም 555 ተገልጋዮች በሰዎች የመነገድ እና በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን የተመለከተ ጥቆማ በመስጠት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደዚሁም ዜጎች በነጻ መስመሩ የህግ ምክርና የተለያዩ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሰዎች የመነገድ እና በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል የሚሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ዜጎችም በህጋዊ መልኩ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እየተሰጠ መሆኑን በመገንዘብ ህጋዊ አማራጭን  እንዲጠቀሙና ህገ ወጦችን እንዲያጋልጡ ጠይቀዋል። 

በሰው የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሄራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ተቋቋሙ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም