ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሀና አርዓያ ስላሴ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ በ2016 በጀት ዓመት ካከናወናቸው ማሻሻያዎች በተጨማሪ በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ  እንደሚሰራ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ማስተዋወቅ ተሞክሮን በመከተል ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

የሎጅስቲክስ አገልግሎቱን ከማቀላጠፍ ባሻገር ለባለሀብቶች ተጨማሪ ማበረታቻዎች እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብና ለ341 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመትም ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎች ሲደረጉ የቆዩ መሆኑን ገልጸዋል።

ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ከመፍጠር አኳያ በተለይ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

ለውጭ ኢንቨስትመንት ተከልክለው የቆዩ የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ የንግድ ዘርፎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ክፍት መደረጋቸውም ትልቅ ውሳኔ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የህግ ማሻሻያዎች፣ ለባለሃብቶች ማበረታቻ የመስጠትና መሰረተ ልማት ማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ እና የዘርፉን አቅም ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ በበጀት ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት  አጠቃላይ 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ከ2015 በጀት ዓመት ሲነጻጸር የ11 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ ጠቅሰው፥ 329 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንም አክለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 227 የውጭ ባለሃብቶች 62 በጥምረትና በሽርክና የሚሰሩ እንዲሁም 40 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቁጥር አንድ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያነሱት ኮሚሽነሯ ይህንኑ ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ከአባል አገራቱ የሚመጣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን እንደሚጨምር አንስተዋል።

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ378 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ329 ፕሮጀክቶች አዳዲስ ፈቃድ ተሰጥቷል። 

በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው ካደረጉ ሀገራት መካከል ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ህንድ፣ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድን፣ ጃፓን፣ ማልታ፣ ቱርኪዬ፣ ፓኪስታንና ሳዑዲ አረቢያ ተጠቃሽ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም