አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት በሀምሌ ወር መጨረሻ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት በሀምሌ ወር መጨረሻ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016 (ኢዜአ)፦ አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት በሀምሌ ወር መጨረሻ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የሥነ-ሕዝብና የጤና ዘርፉን ለማሻሻል ታስበው የሚወጡ ዕቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ መመስረት አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳፊ ገመዴ ለኢዜአ እንዳሉት፣ አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ ህዝብና ጤና ጥናት ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፋይዳዎች አሉት፡፡
ጥናቱ በአመጋገብ ሥርዓት፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ፣ ሥነ ተዋልዶ፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እና የንጹህ መጠጥ ውሀ ተደራሽነት ላይ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቅድመ ዝግጅቱ የጥናቱን ዓላማ ከግብ የሚያደርሱ ጥያቄዎችን ማዘጋጀት፤ የጥናቱን ሥነ ዘዴ መለየት እና ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት በተያዘው ሀምሌ ወር መጨረሻ በማስጀመር በአምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብና ጤና ጥናት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚው፤ የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ተዓማኒና የተሳካ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ከማዘጋጀት ባለፈ ከ500 በላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ በመላ ሀገሪቱ ጥናቱን ማከናወን የሚያስችሉ ከ800 በላይ የናሙና መረጃ ማሰባሰቢያ ቦታዎችን መለየቱን ገልጸዋል፡፡
የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በ1997 ዓ.ም፣ በ2003 ዓ.ም፣ በ2008 ዓ.ም እና በ2013 ዓ.ም የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት መካሄዱ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡