ቀጥታ፡

በክልሉ የመሬት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ በማድረግ በዘርፉ የሚታየውን  ህገ ወጥነት ለመቆጣጠር ትኩረት ተደርጓል

አዳማ፤ሐምሌ 11/2016 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የመሬት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ በማድረግ በዘርፉ የሚታየውን  ህገ ወጥነት ለመቆጣጠር ትኩረት መደረጉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ገለፁ።

የአዳማ ከተማ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም የመጀመሪያው ምዕራፍ የዲጂታል ፕሮጀክት ምረቃና ኦንላይን የመሬት አገልግሎት ስርዓት ይፋ ተድርጓል።

አቶ መስፍን በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የክልሉን ከተሞች ኢኮኖሚያዊና ማህብራዊ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የመሬት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል በማድረግ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለይ የከተሞችን መዋቅራዊ ፕላን በአዲስ መልክ ከማዘጋጀት ጀምሮ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት እውን ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአዳማ ከተማ አስተዳደር በካዳስተርና ኦንላይን የመሬት አገልግሎት ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

''አዳማ ለክልሉ ከተሞች ምሳሌ ናት'' ያሉት አቶ መስፍን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የስማርት አዳማ ፕሮጀክትም ለከተማዋ ልማት እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ ከከተሞች መሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታየውን ሌብነትና ዝሪፊያ እንዲሁም ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቆም ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል።


 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚነስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ የካዳስተር ስርዓት እውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት 20 ዓመታት እንደሆነው ጠቅሰው፤ የለውጡ መንግስት በሰጠው ትኩረት ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም በስፋት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

አዳማ ለሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ በሚሆን መልኩ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥና ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት እውን እያደረገች መሆኗን መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

በዚህም በመሬት አስተዳደር ዘርፍ የሚታየውን ሙስና፣ ሌብነትና ህገ ወጥ መሬት ወረራን ለማስቀረት የተጀመረው ጥረት መጠናከር አለበት ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ሃላፊ አቶ ከድር ማሞ እንደተናገሩት ፤በአዳማ ተግባራዊ የተደረገው ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት የመሬት ሀብቱን በአግባቡና ለተፈለገው ልማት ለማዋል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን አሰራር በክልሉ ከተሞች በማስፋፋት ህገ ወጥነትና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት በስፋት ይሰራል ብለዋል።


 

በአዳማ ከተማ መሬትን ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲውል አስተዳደሩን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ናቸው።

በዚህም ከሊዝ አዋጅ በፊት የነበረውን ነበር ይዞታ ህጋዊ ማድረግ፣ ህጋዊ ይዞታዎችን መመዝገብና ዲጂታል ካርታ መሰጠት ስራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የከተማዋ መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች በሙሉ ዲጂታል በመሆናቸውና መሬት ነክ አገልግሎት በኦላይን በመጀመሩ መሬትና ቤትን በተመለከተ ሽያጭና ግዥ የሚከናወነው በዲጂታል ካርታ ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም