ቀጥታ፡

በክልሉ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው-  አቶ ሽመልስ አብዲሳ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የክልሉ መንግስት በሱሉልታ ከተማ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የደራርቱ ቱሉ ስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመርቋል።

ፕሮጀክቱን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤  ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የስኬት ተምሳሌት በሆነችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ስም ተገንብቶ የተመረቀው ኢንስቲትዩትም የዚሁ ስራ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት አመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ በተለያዩ ችግሮች ሳይጠናቀቅ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ለስፖርቱ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ ስፖርቱን በሳይንሣዊ መንገድ በመምራት ዓለም አቀፍ ተፎካካሪና አሸናፊ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአንድ ጊዜ በ16 የስፖርት አይነቶች 800 ስፖርተኞችን ተቀበሎ የማሠልጠን አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ የስፖርት ማሰልጠኛና የምርምር ኢንስቲትዩቱ ብቁ አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች።

ለሀገር ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ኢንስቲትዩቱ በስሟ በመሰየሙም የላቀ ምስጋናዋን አቅርባለች።

“ኢንስቲትዩቱ ከሰራሁት በላይ ታሪክ ያለው ለወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፣ ዜጎች ለሀገራቸው በቻሉት አቅም ሊያገግሉ ይገባል” በማለትም መልእክቷን አስተላልፋለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም