ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የሚራመድ ጠንካራ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የሚራመድ ጠንካራ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲሰ አበባ፤ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ):- ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የሚራመድ ጠንካራና ተጽእኖ ፈጣሪ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ አዘዘው፤ በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነጋዴዎች ቢኖሩም የተደራጀና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የሚፈለገው ውጤት አልመጣም ብለዋል።
የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች የተቋቋሙበትን ዕድሜ ያህል ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር የምክር ቤቶች ጠንካራ ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን መደገፍና የአባላቱን ቁጠር ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
ከአገራዊ ለውጡ በኃላ ለንግድና ኢንቨስትመንት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የንግድ ህጉ መሻሻል፣ የካፒታል ገበያ መቋቋምና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።
በመሆኑም ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና የስራ ዕድል ለመፍጠር የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስት ለግሉ ዘርፍ ማነቆ የሆኑ የህግና አሰራር ክፍተቶችን በመለየት ማሻሻያ ማደረጉን ጠቅሰው ምክር ቤቱ በግሉ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለይቶ ለፖሊሲ አውጪዎች እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ በአራት ክልሎች አዲስ የተደራጁ ምክር ቤቶችን በአባልነት የሚቀበል በመሆኑ የምክር ቤቱን አባል ምክር ቤቶች ቁጥር ከ18 ወደ 21 ከፍ የሚያደርገው ይሆናል።
በምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።