ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስባለች

አዲሰ አበባ፤ሐምሌ 11/2016 (ኢዜአ):- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሀና አርዓያ ስላሴ የተጠናቀቀውን  በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል።

ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ከመፍጠር አኳያ በተለይ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የህግ ማሻሻያዎች፣ ለባለሃብቶች ማበረታቻ የመስጠትና መሰረተ ልማት ማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ እና የዘርፉን አቅም ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ በበጀት ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት  አጠቃላይ 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ ጠቅሰው፥ 329 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንም አክለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 227 የውጭ ባለሃብቶች 62 በጥምረትና በሽርክና የሚሰሩ እንዲሁም 40 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቁጥር አንድ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያነሱት ኮሚሽነሯ ይህንኑ ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ እቅድ ይዞ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗም ከአባል አገራቱ የሚመጣ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የሚያስችላት እንደሚሆንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም