አየር መንገዱ ከኮምቦልቻ ባህር ዳር ቀጥታ በረራ ሊጀምር ነው

ደሴ ፤ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮምቦልቻ ወደ ባህር ዳር ከተማ ቀጥታ በረራ ሊጀምር መሆኑን  በአየር መንገዱ  የኮምቦልቻ ኤርፖርት ኦፕሬሽን ኃላፊ አስታወቁ።

ኃላፊው አቶ ሰለሞን አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከከምቦልቻ ወደ ባህር ዳር እና ከባህር ዳር ወደ ኮምቦልቻ የነበረው በረራ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

አሁን  መንገደኞች በተደጋጋሚ በረራው ዳግም እንዲጀመር በመጠየቃቸው አየር መንገዱ ከሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየቀኑ በረራውን ዳግም እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

በረራው መጀመሩ ከኮምቦልቻ ወደ ባህር ዳር ለመሄድና  ከባህር ዳር ወደ ኮምቦልቻ ለመምጣት በአዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን ጉዞ እንደሚያስቀር ጠቁመው፤ ይህም የተገልጋዮችን እንግልትና ተጨማሪ ወጭ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡

ተገልጋዮች  ከሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ቀጥታ ከኮምቦልቻ -ባህር ዳርና ከባህር ዳር- ኮምቦልቻ መጓዝ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

የኮምቦልቻ ኤርፖርት ወደ አዲስ አበበ በቀን 6 መደበኛ በረራ ሲኖረው፤ እንደ አስፈላጊነቱ ከ6 በላይ በረራ እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም