ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ለማስተናገድ ስምምነት ፈረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ለማስተናገድ ስምምነት ፈረመች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ከሀምሌ 15-19 ቀን 2016 ዓ.ም ለማስተናገድ የአስተናጋጅ ሀገር ስምምነት ተፈራረመች።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እና የመንግስታቱ ድርጅት የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንዋ ስምምነቱን ፈርመዋል።
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ ስብሰባውን ማስተናገዷ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሰራርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች እንዲጠናከሩ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ጸሃፊዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስብሰባውን ለማስተናገድ ያላትን ቁርጠኝነት እና ሚና አድንቀዋል።
ሁለቱ ወገኖች ለዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ለማሰባሰብ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማነሳሳት ጉባዔው ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሦስተኛውን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ አስተናግዳለች።
ጉባዔው ለዘላቂ ልማት ግቦች ፋይናንስ ለማፈላለግ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍን ያስቀመጠውን የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብር ማፅደቁ ይታወሳል።
ከመጭው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብርን አፈፃፀም ይገመገማል።
በቀጣይ ዓመት በስፔን ለሚካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃው አመላክቷል።