የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ ልጆች ጥራት ያለው ትምህርትን እንዲያገኙ አስችሏል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ ልጆች ጥራት ያለው ትምህርትን እንዲያገኙ አስችሏል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 11/2016 (ኢዜአ)፦ በትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ ልጆች ጥራት ያለው ዘመናዊ ትምህርትን እንዲያገኙ ማስቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሶስት ሚሊዮን በላይ የገጠር ነዋሪዎች በአማራጭ ቴክኖሎጂ የፀሐይ ሐይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መደረጋቸውም ተገልጿል።
በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የተመራው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በሶማሌ እና ሐረሪ ክልሎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶችን መርቀው ስራ በማስጀመር ላይ ናቸው።
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በምስራቅ የአገሪቷ ክልሎች ተመርቀው ወደ ስራ የገቡት የፀሐይ ሐይል ፕሮጀክቶች ሚኒስቴሩ የገጠሩን ህብረተሰብ የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት የጀመራቸው ተግባራት ማሳያዎች ናቸው።
በተለይም በትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ልጆች ጥራት ያለው ዘመናዊ ትምህርትን አግኝተው ለአገር አለኝታ እንዲሆኑ ያስችላሉ ብለዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የገጠር የአመራር አካላት፤ መምህራንና ህብረተሰቡ ፕሮጀክቶቹ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከዋና የኤሌክትሪክ ማሰራጫዎች ርቀው የሚገኙ የገጠር የህብረተሰብ ክፍሎችን የኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በቴክኖሎጂ የታገዙ ከ350 በላይ የሶላር አማራጭ የሃይል ምንጮችን በገጠራማ የአገሪቷ ክፍሎች በመትከል ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በተለይም በ156 ትምህርት ቤቶች እና መለስተኛ የጤና ተቋማት የፀሐይ ሐይል ተጠቃሚ በመሆናቸው የገጠሩን ህብረተሰብ ሁለንተናዊ ህይወትና አኗኗር እየለወጠ መሆኑን አውስተዋል።
የፀሐይ እና የውሃ ሃብትን በአነስተኛ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የገጠሩን ህብረተሰብ ፍትሐዊ የኢነርጂ ተጠቃሚ ከማድረግ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂው በአነስተኛ የመስኖ ስራዎች ላይ በመተግበር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ይሰራል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ የተገኙትን አበረታች ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከተለያዩ አጋር አካላት እና ዩኒሴፍን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
"በቀጣይም አማራጭ የሶላር ኃይልን በትላልቅ ተቋማት ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ከ600 እስከ 700 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችሉ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችን በገጠራማ የአገሪቷ አካባቢዎች የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴሩ የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ወልዱ ናቸው።
በገጠር የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በ2030እ.ኤ.አ አብዛኞዎቹ የገጠር የህብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ዋና ዋና የማሰራጫ ተቋማት ግንባታም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመጠቆም።
ዛሬም በሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) የተመራው ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞንና ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች ተገኝቶ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ይመርቃሉ።