ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ነው    

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/ 2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ገለጹ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ ዓለምን ሥጋት ውስጥ እየከተተ ለሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ፈታኝ ኩነት የአገራትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ በመረዳት ዜጎችን በማስተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ወደ ተግባር መግባቱን አንስተዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ጭምር ተምሳሌት ለመሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያከናወነች መሆኑ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን የሚያሳይ ጭምር ነው ብለዋል።

  በዘንድሮ ዓመት ይህ መርሃ-ግብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ፍስሐ፤ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፖርት ሱዳን ችግኝ መትከላቸው የዚሁ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያነሱት።  

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ችግኝ በመላክ ለአረንጓዴ አካባቢ ልማት መጠናከር የበኩሏን ስትወጣ ቆይታለች። 

መርኃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያለውን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ከግምት በማስገባት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን የራሱ ባንዲራ ፕሮጀክት ማድረጉም ይታወሳል። 

በዘንድሮው የ2016 ዓ.ም የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገሪቱ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም