የቀርከሃ ተክልን ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 10/2016 (ኢዜአ)፦የቀርከሃ ተክልን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የትኩረት መስክ በማድረግ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሚያከናውነው የተቀናጀ የቆላ ቀርከሃ ልማት የሚሆን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ማጣላ ሔምቤቾ ቀበሌ ዛሬ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የቀርከሃ ደን በምድሯ በመያዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት ።

ተክሉ የአካባቢን ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ ማህበረሰቡ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች የሚያውለው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የቀርከሃ ተክልን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የትኩረት መስክ በማድረግ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከሀገር በቀል ዝርያዎች መጠበቂያ ስልት አንዱ ነባር ደኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ መሆኑን አንስተው ዝርያዎቹን በስፋት መትከል ደግሞ ሌለኛው መሆኑን ጠቁመዋል።

የቆላ ቀርከሃም ከሀገር በቀል የዕፅዋት ዝርያዎች የሚመደብ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ሞቱማ ይህንኑ ለማስፋት በቦሎሶ ሶሬ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላም በሞዴልነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ደን ልማት የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው፤ ተከላው የተካሄደበት ሥፍራ እጅግ የተጎዳና ገላጣማ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ከሥነ አካላዊ ሥራዎች ጀምሮ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ነው" ብለዋል።

ተክሉ እድገቱን ሲጨርስ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ማስገኘት የሚችል በመሆኑ ማህበረሰቡ በባለቤትነት እና በዘላቂነት ሊንከባከበውና ሊጠብቀው እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሀገራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንደገለጹት፤ መርሐ ግብሩ ከዓመት ወደ ዓመት አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸውን አሰራሮች ይዞ እየመጣ ነው።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርትና የቀርከሃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ብርቱካን ደሴ፤ የቆላ ቀርካሃ ዝርያውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማምጣትና በምርምር በመደገፍ ተክሉን ከአካባቢው ጋር የማላመድ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የቦሎሶ ሶሬው የቆላ ቀርከሃ ፕሮጀክት በሞዴል ደረጃ የሚደገፍ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአካባቢው ተፈጥሯዊ ሥነ ምህዳር እንዲያገግም ከማድረግ ባለፈ ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማምጣት እንዲችል እየሰራን ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በቀርከሃ ሥራ ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ከ600 በላይ ወጣቶችን ማሰልጠን መቻሉንም ገልፀዋል።

ተከላው የተከናወነበት ማጣላ ሔምቤቾ ቀበሌ ነዋሪ መምህር አክሊሉ ደምሴ፤ የአረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የተራቆቱ መሬቶች ወደ አረንጓዴነት እየተቀየሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የቆላ ቀርከሃ የተተከለበት ሥፍራ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ የተጎዳና ምንም ጥቅም ሊሰጥ የማይችል እንደሆነ የገለፁት መምህር አክሊሉ፤ "አሁን ላይ ቦታው በሚገባ ተስተካክሎ ችግኝ በመተከሉ ተደስቻለሁ" ብለዋል።

በተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ደን ልማት፣ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የወላይታ ዞን አመራር አባላት እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም