የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር በኃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር በኃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በማጠናከር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የተ.መ.ድ የልማት መርኃ ግብር የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል 'ቅደመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም' የተሰኘ ኢኒሼቲቭ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
በኢኒሼቲቩ በዓለም ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ የሆኑ 30 ሀገራት የታቀፉ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 13ቱ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።
በዚህ ኢኒሼቲቭ ትግበራ ዙሪያ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች የተገኙበት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነትና አስቻይ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አቅሟን ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል።
አካታችና ሁሉን አቀፍ ጠንካራ ሥርዓት ለመዘርጋት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት እንደሚሻ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለ'ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም' ኢንሼቲቭ ትግበራና ተፈፃሚነት በትኩረት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።
ጎን ለጎንም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ዘላቂ ምላሽ የመስጠትና የተፈጥሮ ኃብትና የአካባቢ ጥበቃ እያከናወነች ነው ብለዋል።
ይህንን ጥረት ለማስቀጠል የፋይናንስ ድጋፍን ጨምሮ የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በመገንባትም በአየር ፀባይ መለዋወጥ ሳቢያ በኃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከልና ምርታማነትን ለመጨመር ትኩረት መሰጠቱን ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበርሃ አንበጣ አደጋዎች የምግብ ዋስትና ችግር እያስከተሉ ነው ብለዋል።
በዚህም የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል ለችግሩ ምላሽ የሚሰጥ በቴክኖሎጂና በወቅታዊ መረጃ የታገዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዘርጋት አይተኬ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
አካታች፣ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቷን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ የልማት መርኃ ግብር ተወካይ ሳሙኤል ግባይዴ፤ የ"ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም" ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን መሰል ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ለሆኑ አገራት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢኒሼቲቩ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በተለይ በሴቶች ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን የሚያስተከትለውን አደጋ ለመቀነስና ለመከላከል እንደሚያስችል ነው ያነሱት።
የጋራ ፈተናን ወደ ዕድል መለወጥና ዘላቂ የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኢኒሼቲቩን ትግበራ ውጤታማ ለማድረግም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2027 ለሚተገበረው የ"ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም" ኢኒሼቲቭ ትግበራ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።