ቀጥታ፡

በአብዛኞቹ ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እስከ ነሐሴ 30 ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦በአብዛኞቹ ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እስከ ነሐሴ 30 ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። 

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በድሬደዋና በክልሎች የሚካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና ሐረር ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መድረክ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና ኮሚሽነሮች ከዛሬ ጀምሮ ሥምሪት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአብዛኞቹ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።  

የሙቀት መጠናቸው ከፍተኛ በሚሆንባቸው እንደ አፋር ክልል ጥቅምት ወር መጀመሪያ አጀንዳ ማሰባሰብ ለማካሄድ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

በአብዛኞቹ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን በማጠናቀቅ፤ በትግራይና አማራ ክልሎች ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል። 

 በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት በምክክሩ ለመሳተፍ ይሁንታቸውን ካሳወቁ "ደኅንነታቸው ተጠብቆ በምክክሩ እንዲሳተፉ የማስደረግ አቅም አለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

50 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ አጀንዳዎችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በምክክሩ ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ በትግራይና አማራ ክልሎች ሁኔታዎችን በማመቻቸት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ከ1 ሺህ 800 በላይ የተባባሪ አካላት ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ የተሳታፊ ልየታም በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዩነትና አለመግባባትን በውይይት ለመፍታት ሂደቱን እንዲያመቻች በ2014 ዓ.ም በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺህ ተሳታፊዎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት መቅረባቸውም እንዲሁ። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም