በክልሉ 54 ሺህ ቶን የሚጠጋ የቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

ቦንጋ፤ ሐምሌ 10/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 54 ሺህ ቶን የሚጠጋ የቅመማ ቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን የክልሉ ቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት ክልሉ ከቡና በተጓዳኝ በቅመማቅመም ልማት ትልቅ  አቅም አለው።


 

አቅሙን በመጠቀም በ2016 በጀት ዓመት 54 ሺህ 366 ቶን የቅመማቅመም ምርቶችን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 53 ሺህ 911 ቶን ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም የዕቅዱ 99 በመቶ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ2015 በጀት ዓመት ከቀረበው ደግሞ በ10ሺህ 811 ቶን  ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

ልማቱም ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ  ማሳ ላይ መስፋፋቱን አመልክተዋል ። 

ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በቀጣይ የግብይት ስርዓቱን ህጋዊ ማድረግ፣ እሴት መጨመር፣ የተጠናከረ የገበያ ትስስር መፍጠርና ለምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ትኩረት መስጠት መሆኑን ገልፀዋል።

ክልሉ ካለው እምቅ አቅምና ማሳ ሽፋን አኳያ  በ2017 በጀት ዓመት 56 ሺህ ቶን የቅመማቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በክልሉ በሰፊው ከሚመረቱ የቅመማቅመም አይነቶች መካከል፥ ኮረሪማ፣ እርድ፣ ዝንጅብል፣ ቁንዶ በርበሬ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ቅመማቅመም በሰፊው ከሚለማባቸው የካፋ ዞን ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው ጎባ በርካታ አርሶ አደሮች በዘርፉ ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።

በወረዳው የኦጊያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደለ በቀለ ከአንድ ጥማድ በላይ የኮረሪማ ማሳ እንዳላቸው ገልፀው፣ ከዚህም ጥሩ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በልምድ በሚያመርቱበት ወቅት ከልፋት ውጭ ብዙም ጥቅም እንደማያገኙ አስታውሰዋል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚሰጣቸው ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው መስራት በመጀመራቸው ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማቅረብ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ።


 

አንድ ሄክታር የኮረሪማ ማሳ እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የጉንድራገራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ዳምጠው ገብሬ፣ ኮረሪማ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በኑሯቸው ላይ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም