የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦ የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በተለይም በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር )ገለጹ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የተመሩ የአመራርና ባለድርሻ አካላት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞንና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ተገኝተው የግድቤን በደጄ (የጣሪያ ላይ ውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክት)፣ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የተጠናቀቁ የውሃና ኢነርጂ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት ላይ ናቸው።
የዝናብ ውሃን ከጣሪያ ላይ በዘመናዊ መንገድ በማሰባሰብ የውሃን ችግር በዘላቂነት ለማቃለል የሚያስችል የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በሚኒስትሩ የተመራው ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በምስራቅ የአገሪቷ ክፍል ግድቤን በደጄ መርሃ ግብር የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መርቆ ስራ እያስጀመረ ነው።
ተጠናቀው ለአገልግሎት የተዘጋጁት መሰል ፕሮጀክቶቹ በቁጥር 82 ሲሆኑ፤ እነዚህም ከ65 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፤ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት፤ የግድቤን በደጄ መርሃ ግብር በዘመናዊ መንገድ የጣሪያን ውሃ በማሰባሰብ የውሃ ተደራሽነትን በማሳደግና የዘርፉን ችግር በማቃለል ረገድ ሁነኛ መፍትሄ እያመጣ ነው።
የግድቤን በደጄ ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበሩትን የውሃ ማቆር እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በማሻሻል በጎንደር እና በቦረና በሙከራ ደረጃ መተግበር ተጀምሯል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ መሠረታዊ ግብ በአገሪቷ ውሃ አጠር አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የውሃ ችግር ማቃለል መሆኑንም አክለዋል።
በ2015 ዓ.ም በ87 ትምህርት ቤቶች ላይ ፕሮጀክቱ መተግበሩን ጠቅሰው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ደግሞ በ120 ትምህርት ቤቶች ዕውን በማድረግ በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የውሃ ችግር መፍታት መቻሉን ነው ያስረዱት።
የጠብታ ውሃ ማሰባሰቢያ ፖንዶቹ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ በመሆናቸው ጎን ለጎን የኢነርጂ ችግርንም እያቃለሉ ይገኛሉ ብለዋል።
የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ንፅህናቸው ጠብቀው በምገባ መርሃ ግብር እንዲሳተፉ ከማስቻል ባሻገር በትምህርት ቤቶች የሚሰበሰበው ውሃ አትክልትና ፍራፍሬን ወደ ማምረት በማሸጋገር በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እየደገፈ መሆኑንም አብራርተዋል።
በቀጣይም የአርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ከብቶች የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ይህን ውጤታማ ፕሮጀክት በመላው አገሪቷ ክፍል ከማስፋፋት ጎን ለጎን ቴክኖሎጂው ቀላል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የዝናብን ውሃ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል።
ለዚህም ቴክኖሎጂውን ቤት ለቤት የሚያስፋፉ በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በማሰልጠን የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል በግድቤን በደጄ ፕሮጀክት የተገነቡ የጠብታ ውሃ ማሰባሰቢያ ፕሮጀከቶች በ18 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ4ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ ጀደኔ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ፋራህ አዋሌ በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎች ቀደም ሲል ውሃን በጀሪካንና በኮዳ ከቤት ይዘው በመምጣት ይማሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን የውሃም የኢነርጂም ችግር ተፈቶልናል ብለዋል።
ዛሬ ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ደንገጎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሌላኛው ነው።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አሪፍ ራህማቶ በበኩላቸው፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ተማሪዎች ንፅህናቸውን ለመጠበቅ እና የትምህርት ቤቱ የምገባ ስርዓት እንዳይስተጓጎል ያስችላል ብለዋል።
ይህን ፕሮጀክት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።