ቀጥታ፡

በድሬዳዋና በሶስት ክልሎች በቀጣይ ሳምንት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋና በሶስት የተለያዩ ክልሎች በቀጣይ ሳምንት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሊጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ፤ በቀጣይ የሚካሄዱትን የአጀንዳ ልየታ መድረኮች በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመሆኑም በቀጣይ ሳምንት በድሬዳዋ አስተዳደር እንዲሁም በሀረሪ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ይካሄዳል ብለዋል።

ለዚህም ስራውን ለማስተባበር የኮሚሽኑ ሙያተኞችና ኮሚሽነሮች ወደ አካባቢዎቹ ስምሪት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለምክክር ሂደቱ የክልል መስተዳድርና ተባባሪ አካላት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በድሬዳዋ እና በ10 ክልሎች እስከ ነሃሴ 30 የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የኮሚሽኑ ሃላፊዎች በትግራይና አማራ ክልሎች ከአመራሮች ጋር ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችሉ ውይይቶችን ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከ1 ሺህ ለሚበልጡ አስተባባሪዎች ስልጠና በመስጠት የተሳታፊዎች ልየታ እየተካሔደ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከግንቦት 21  እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም መካሔዱ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ልዩነትና አለመግባባትን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተጀመረው የአገራዊ ምክክር ሂደት በአሁኑ ወቅት የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

በምክክሩ ላይ በሀገራዊ የባለቤትነት ስሜት የመላው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ፣ በምክክሩ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ባለድርሻ አካላት መካተትን ማረጋገጥና ሙሉ ተሳትፎ መኖር፣ የፓለቲካ ፍቃደኝነት የአገራዊ ምክክርን ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊ ከሆኑ ሁነቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም