ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ አደጋዎችን ምላሽ ለመስጠት የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ አደጋዎችን ምላሽ ለመስጠት ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ። 

የተ.መ.ድ የልማት መርኃ ግብር ኢትዮጵያን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ በሆኑ አገራት የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል'የቅደመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም' የተሰኘ የአምስት ዓመት ኢኒሼቲቭ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ኢኒሼቲቭ ትግበራ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ መንግስታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነትና አስቻይ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አቅሟን ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመዘርጋት ግን የባለድርሻ አካላትን ቅንጅትና ትብብር የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የ'ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች ለሁሉም' ኢንሼቲቭ ትግበራና ተፈፃሚነት በትኩረት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአካባቢ መራቆትን ለመመለስ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል። 

ይህንን ጥረት ለማስቀጠል የፋይናንስ ድጋፍን ጨምሮ የአጋር አካላት ትብብር እንደሚሻ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበርሃ አንበጣና መሰል ተደጋጋሚ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለምግብ ዋስትና ችግር እየዳረጉ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም ችግሩ የሚያስከትለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል ለችግሩ ምላሽ የሚሰጥ በቴክኖሎጂና በወቅታዊ መረጃ የታገዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዘርጋት ያለውን አይተኬ ሚና ጠቅሰዋል።

አካታች፣ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት። 

በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ የልማት መርኃ ግብር ተወካይ ሳሙኤል ግባይዴ፤  የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን መሰል ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ለሆነ አገራት የተቀናጀ አደጋ ለመከላከል ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ኢኒሼቲቩ የጋራ ኃላፊነት ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም በተለይም ሴቶች ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን የሚያስተከትለውን አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ነው ያነሱት።

የጋራ ፈተናን ወደ ዕድል መለወጥና ዘላቂ የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ ትግበራ ላይ የሚገኘው ኢኒሼቲቩ ውጤታማነትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም