የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ዓመት መስከረም 10 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ዓመት መስከረም 10 ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣዩ የውድድር ዓመት መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጀምር የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ።
ማኅበሩ ውድድሩን በተጠቀሰው ጊዜ እንደሚጀመር ለተሳታፊ ክለቦች ማሳወቁን ገልጿል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት 19 ክለቦች ተሳታፊ ናቸው።
የትግራይ ክለቦች በ2017 ዓ.ም ውድድር ከማቆማቸው በፊት ወደነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሑል ሽሬና መቀሌ ሰብዓ እንደርታ በሊጉ ላይ ይሳተፋሉ።
ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት አርባ ምንጭ ከተማና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በቀጣይ ዓመት በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።
በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን በ19 ክለቦች መካከል ውድድር ተደርጎ 5 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንደሚወርዱ ተገልጿል።
በ2018 የውድድር ዓመት ሁለት ክለቦች ደግሞ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚያድጉም እንዲሁ።
ይህንንም ተከትሎ በ2018 ዓ.ም ሊጉ ወደነበረበት 16 ክለቦች እንደሚመለስ ነው ማኅበሩ ያስታወቀው።
የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።