ቀጥታ፡

የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2016 (ኢዜአ)፦የአርሶ አደሮችን ምርታማነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ግብርናን የሚያዘምኑ ሁለት የዲጂታል የአሠራር መተግበሪያዎችን ይፋ አድርጓል።


 

የዲጂታል መተግበሪያዎቹም የዲጂታል ገበያ ትስስር (Digital Market Linkage Platform) እና ኢ- ቮውቸር 2.0 (Automation Of Input Voucher System) የሚባሉ ናቸው።

በይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር)፤ አርሶ አደሮችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሰፋት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ይፋ የተደረጉት መተግበሪያዎች የግብርና ምርት ግብዓትና ሥርጭትን እንዲሁም ግብይትን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያሰችሉ መሆኑን ገልፀዋል።     

ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ በዛሬው እለት ይፋ የተደረጉት ዲጂታል ሲስተሞች በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል ግብርናና ገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር ግሩም ከተማ(ዶ/ር)፤ ኢ-ቮውቸር 2.0 (Automation Of Input Voucher System) የግብርና ግብዓት ሥርጭት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከዚህ ቀደም የግብዓት ሥርጭት በወረቀት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከእጅ ንክኪ ነፃ ሆኖ በዲጂታል መንገድ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

የዲጂታል ገበያ ትስስር (Digital Market Linkage Platform) ደግሞ ገዥና ሻጭን በቀጥታ የሚያገናኝ መሆኑን ገልጸው፤ ሕገ-ወጥ ደላላን ከሰንሰለቱ የሚያስወጣ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ትኩረቱን በአፍሪካ ምግብ ሥርዓት ላይ አድርጎ የሚሰራው (Sustainably Growing Africa's Food Systems) /AGRA/ ካንትሪ ዳይሬክተር ይሄነው ዘውዴ (ዶ/ር)፤ ተቋሙ በ12 የአፍሪካ አገራት ግብርናን ለማዘመን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያም የግብዓት አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም የምርት ግብይት እንዲያድግ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም