ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ተስማምተዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ ፈርመዋል፡፡
በዚህም በሁለቱ ሀገራት ለሚደረግ ግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ማለትም ድርሃምና ብር ለመጠቀም ነው ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡
ሁለቱ አካላት ለተግባራዊነቱ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚህ ወቅት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከኢትዮጵያ ታላላቅ የንግድ አጋሮች አንዷ መሆኗንና የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ገልጸዋል።
በዚህም ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረት ቀጣይነት ያለው ልማትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን ያሳያል ማለታቸውን ባንኩ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።