ቀጥታ፡

ዳያስፖራዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በቀላሉ ተሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል ፓኬጅ እየተቀረጸ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2016(ኢዜአ)፦ከክልሎች ጋር በመተባበር ዳያስፖራዎችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በቀላሉ ተሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል ፓኬጅ እየተቀረጸ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ። 

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው። 

ተቋሙም ለዳያስፖራው የሚሰጠውን ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችን የማዘመንና ተደራሽነታቸውን የማስፋት ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ውጤታማ እንዲሆን በምን አይነት የኢንቨስትመንት አማራጮች  ላይ መሰማራት እንዳለበት ጭምር ለማማከር የሚያስችል ሥርዓት እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

ጎን ለጎንም ከክልሎች ጋር በመተባበርም ዳያስፖራውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፓኬጅ የመቅረጽ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ፓኬጁ ክልሎች ያሏቸውን አቅሞች በዝርዝር ለዳያስፖራ አባላት የሚያቀርቡበትና ዳያስፖራውም በቀላሉ ይህንን በመገምገም ወደ ኢንቨስትመንት የሚገባበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

ይህም ዳያስፖራው በየትኛው የአገሪቱ አካባቢ በኢንቨስትመንት ልሰማራ? በየትኛው የኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት አለብኝ ? የሚሉትን ጥያቄዎች በቀላሉ ለመመለስ ያስችላልም ነው ያሉት።   

ይህም ብቻ ሳይሆን አገሪቱም የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ በሙሉ አቅም ወይንም አሟጦ ለመጠቀምና አገሪቱ ለመድረስ ያሰበችውን ብልጽግና እውን ለማድረግ መደላደል ይፈጥራል ብለዋል። 

በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ አገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከሰሞኑ ለኢዜአ መግለጹ ይታወሳል። 

በዚሁ በጀት ዓመት 273 የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ለማስቻል ተጨባጭ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጸው ይኸው ተቋም፤ ከእነዚህም ውስጥ 50 የዳያስፖራ አባላት ወደ ሥራ በመግባት ለ3 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቁሟል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም