በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2016(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ከ298 ሺህ ቶን በላይ ቡና 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ጥራት ያለው የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ 298 ሺህ 500 ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።
ለውጭ ገበያ የተላከው የቡና ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ50ሺህ 500 ቶን ጭማሪ ማሳየቱን ገልፀዋል።
በዓመቱ ለውጭ ገበያ የተላከው የቡና ምርት በጥራትና በመጠን ከፍተኛ እንደነበርም አስረድተዋል።
አርሶ አደሩ ያመረተውን የቡና ምርት የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር በቀጥታ ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ማድረግ ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ አርሶ አደሩ ከቡና ምርት የሚያገኘውን ገቢ ከ40 በመቶ ወደ 80 በመቶ ማሳደግ መቻሉም ተገልጿል።