ቀጥታ፡

መንግስት ያቀርባል፤ ወጣቶች ያመርታሉ፤ አርሶ አደሮችም እየተጠቀሙ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለዘመናዊ የንብ ቀፎ ግብዓት እያቀረበ፤ ወጣቶች እያመረቱና አርሶ አደሮችም በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው እንዲጠቀሙ ምቹ የገበያ ሰንሰለት መፈጠሩ ተገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ዞን ከ250 ሺህ በሚልቁ ዘመናዊ ቀፎዎች በዓመት በአማካይ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ማር እያመረቱ መሆኑም ታውቋል።

ለንብ ማነብና የማር ምርት ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በሚቀርብላቸው ግብአት ዘመናዊ ቀፎዎችን ወጣቶች እያመረቱና አርሶ አደሮችም በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው እንዲጠቀሙ ምቹ የገበያ ሰንሰለት ተፈጥሯል።

በዚህ ስኬታማ የልማት ሰንሰለት ውስጥ ካሉ ወጣቶች መካከል አልዓዛር አሠፋ፣ ወንዴ ገዛኸኝ እና ሸሪፍ ሽፋ ፤ መተሳሰብና መደጋገፍ ያለበት በመሆኑ በደስታ እየሰራን እየተጠቀምንም ነው ብለዋል። 


 

መንግስት ጣውላና መሰል የዘመናዊ ቀፎ መስሪያ ግብዓት ያቀርባል፤ ወጣቶች ያዘጋጃሉ፤ ንብ አናቢ አርሶ አደሮች ደግሞ ቀፎውን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ማር በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ልማት የበርካታ ወጣቶች ህይወት እየተለወጠ ሀገርም በሌማት ትሩፋት እየተጠቀመች መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በኢሉ አባቦራ ዞን በንብ ማነብ የተሰማሩት አርሶ አደር ታደገ ተካልኝ እና መሃመድ ኑር ኡስማን፤ ጥራት ያለው ዘመናዊ ቀፎ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል፤ በዘመናዊ ቀፎ ብዛትና ጥራት ያለው ማር በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢሉ አባቦራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳልካቸው ተፈሪ፤ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማሰማራት የሥራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ በዘመናዊ የንብ ቀፎ ምርት የተደራጁ 26 ማህበራት ወደ ሥራ ገብተው ለንብ አናቢዎች እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ለአርሶ አደሮች የሚቀርበው ዘመናዊ ቀፎ ማር ምርታቸውን ማሳደጉን ገልጸው፤ በዚህም ከለውጡ በፊት ሶስት ሺህ ቶን የነበረው የማር ምርት ወደ 12 ሺህ ቶን አድጓል ብለዋል፡፡

የኢሉ አባቦራ ዞን ለማር ምርት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ልማትና ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም