በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መልቀቂያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መልቀቂያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2016 (ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መልቀቂያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።
የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ማጠናቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፈተናው ከሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት የፈተና አሰጣጡን ተመልክተዋል፡፡
ፈተናው በኮምፒውተር(online) እና በወረቀት እየተሰጠ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ 12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ መልቀቂያ ፈተና በመላው ሀገሪቱ በጥሩ ሁኔታ እየከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፈተና አሰጣጡ የተሳካ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
ይህም የፈተና አሰጣጡ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት ለተማሪዎች አስፈላጊው ገለፃ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም ተፈታኞች በፈተና ወቅት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እና መብት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በፈተና ቆይታቸው ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ህገ-ደንቦችን በሚመለከት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም በዩኒቨርሲቲው 4 ሺህ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናቸውን እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡