በሰሜን ሸዋ ዞን ከ98 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን ከ98 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

ደብረ ብርሃን ፤ ሐምሌ 9/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት 98 ሺህ 831 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈን መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃለፊ አቶ ሰለሞን ቀለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2016/17 የመኸር ወቅት በዞኑ 497 ሺህ 525 ኼክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ከዚህ ውስጥ 198 ሺህ 818 ኼክታር መሬት የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በጤፍ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ ገብስ፣ ስንዴና በማሾ ሰብሎች የሚለማ ነው ብለዋል።
የመኽር ሰብል ልማቱ በትራክተር ታግዞ እየተከናወነ ሲሆን እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ማሽላ፣ ስንዴ፣ የቢራ ገብስና ባቄላን ጨምሮ 98 ሺህ 831 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።
ቀሪውን መሬት በወቅቱ በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን በ2016 የምርት ዘመን በሄክታር 29 ነጥብ 5 ኩንታል የነበረውን ምርታማነት ወደ 34 ነጥብ 5 ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ምርታማነትን ለመሳደግም በገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች አማካኝነት ከ703 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና 3 ሺህ 700 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል።
እንዲሁም በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልፀዋል።
ከየዞኑ አርሶ አደሮች መካከል በአጎለና ጠራ ወረዳ ጨኪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደረጀ ዓለሙ እንዳሉት፤ በዚህ የመኽር ወቅት ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት በሰብል ለማልማት እየሰሩ ነው።
እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴም ግማሽ ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ክላስተር በዘር የሸፈኑ ሲሆን ቀሪውን መሬትም በዘር የመሸፈን ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
አርሶ አደር አሸናፊ መልካ በበኩላቸው፤ አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በስንዴ ሰብል ማልማት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ2016/17 በመኸር ከሚለማው መሬት 17 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።