የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ጭፍጨፋን ትርጉም ባለው መልኩ ቀንሷል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ጭፍጨፋን ትርጉም ባለው መልኩ ቀንሷል
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 08/2016 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ጭፍጨፋን እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ ።
የኢትዮጵ ደን ልማት አመራር አባላትና ሠራተኞች በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱሎ ቀበሌ ኩዪዋታ ተፋሰስ ላይ በሚገኝ ከፍታ ስፍራ ላይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በዚህ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በደን ጭፍጨፋ ትርጉም ባለው መልኩ ቀንሷል።
"በተለይም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ንቅናቄ የተነሳ የደን መጨፍጨፍ ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ በየአመቱ የሚጨፈጨፈው የደን መጠንም እንዲሁ እየቀነሰ ነው" ብለዋል።
ሰዎች ከጊዜ ወደጊዜ ደንን መጨፍጨፍ ሊያመጣ ስለሚችለው ጉዳት በውል እየተረዱ መምጣታቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ደን በመጨፍጨፍ ፋንታ ለማገዶና ለግንባታ የሚውሉ የዛፍ ችግኞችን በጓሯቸውና በሌሎች ይዞታዎች ላይ የመትከል ልምድ እያደበሩ መሆናቸውን ተናገረዋል።
በደን ልማት ሥራ ውስጥ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ እንዲፀድቅ የማድረግ ግንዛቤ እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው በዚህም እንደ ሀገር የፅድቀት መጠን ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አውስተዋል።
በተለይም የአየር ንብረትን መቆጣጠርና ለምግብነት የሚውሉ እንዲሁም የጎርፍ መሸርሸርን የሚከላከሉ ችግኞች መተከላቸውን አንስተው የፅድቀት መጠናቸው ከ86 በመቶ በላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል ደን፣ አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽታዬ ዩሙራ በበኩላቸው "በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል" ብለዋል።
ይህም በክልሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን የተናገሩት አቶ ሽታዬ ለአብነት የክልሉ ደን ሽፋን መጨመሩንና የተጎዱ መሬቶች ወደ ምርታማነት እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ዘንድሮ ዓመትም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው በተለይም ለጥምር ግብርና የሚያግዙ ችግኞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተከላው ከተሳተፉ የተቋሙ ሰራተኞች መካከል አቶ ሮቤል ከተማ ለተከታታይ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ በተከላ መሳተፋቸውንና በሚታየው ለውጥም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል
በዛሬው ዕለት ብቻ 40 የሚሆኑ ችግኞችን እንደተከሉ ጠቅሰው ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ በመሆኑ መትከሌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብለዋል ።
"በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጣውን ችግር ከመከላከል ረገድ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤታማ ነው" ያሉት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ናቸው።
"በተለይም በምግብ ሰብል ራሰን ለመቻልና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ጠንካራ ተሳተፎ ሊያደርግ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም ከሲዳማ ክልል የተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካት ተገኝተዋል ።