ቀጥታ፡

በክረምት ወቅት አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በበጎ ፈቃድ በማገዝ ወገናዊ አለኝታነታችንን ማሳየት ይገባል - አቶ ቢኒያም በለጠ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2016(ኢዜአ)፦ በክረምት ወቅት አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በበጎ ፈቃድ በማገዝ ወገናዊ አለኝታነታችንን ማሳየት ይገባል ሲሉ የመቄዶንያ መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ ገለጹ።

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር በክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተመሰረተ 13 ዓመታትን ያስቆጠረው መቄዶንያ የሀገር ባለውለታዎችን ጨምሮ በዕድሜ ማምሻ ላይ ደጋፊና ጧሪ ላጡ እንዲሁም ለአዕምሯዊ ችግር ለተዳረጉ ወገኖች መጠጊያ እና መጦሪያ የሆነ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው።

በዚህም ለሺዎች አቅመ ደካማ ዜጎች መጠጊያ እና ማረፊያ ሆኗል።

ማህበሩ ቅርንጫፎችን እያሰፋ አሁን ላይ በሀገሪቱ 27 ከተሞች 7ሺህ 500 አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን የሆኑ ወገኖችን ሰብስቦ እየተንከባከበ ይገኛል።

የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ ለኢዜአ እንዳሉት መቄዶንያ ያለምንም የገቢ ምንጭ በቅን ግለሰቦች ድጋፍ ብቻ ዕልፍ ዜጎች ከአስከፊ ሕይወት ወጥተው በክብር እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል።

ማህበሩ አሁን ላይ ተደራሽነቱን እያሰፋ መሆኑን ገልጸው፤ የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 20ሺህ ማዕከላትን ደግሞ ወደ 120 ለማሳደግ በክልሎች በየወሩ አንድ ቅርንጫፍ የመክፈት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

መቄዶንያን ከገንዘብ እና ከቁሳቁስ ባሻገር በማዕከሉ በመገኘት ለተገልጋዮች ሁሉን አቀፍ እንክብካቤ የሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉ ገልጸዋል።

መቄዶንያን ለማገዝ ሰው መሆን በቂ ነው ያሉት አቶ ቢኒያም፤ በተለይም በክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወገኖች መቄዶኒያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የክረምት ወቅት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ወገኖች ከርሃብና እርዛት ባሻገር ለተደራራቢ ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው ማህበሩ በተለይም በክረምት ወቅት የጎዳና ላይ ሰዎችን እንደሚያነሳ ገልጸዋል።

ይህም በትምህርት ዓለም የቆዩ ወጣቶችን ጨምሮ የበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ሁሉን አቀፍ አገልግሎትን እንደሚሻ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃን ማህበረሰቡን ስለበጎ ፈቃድ የማስገንዘብ እንዲሁም የመቄዶኒያ አገልግሎትን በስፋት በመዘገብ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም አቶ ቢኒያም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም