ከቡና ምርት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ በጥናት የተደገፈ ሥራ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ከቡና ምርት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ በጥናት የተደገፈ ሥራ ይሰራል
ሚዛን አማን ፤ሐምሌ 8/2016 (ኢዜአ)፦ከቡና ምርት የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሳደግ ከትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን በጥናት የተደገፈ ሥራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር አስታወቀ።
ማኅበሩ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና አዘጋጆችና አቅራቢዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የቡና ሥራ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችና መፍትሄዎችን ለማመላከት በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ የቡና አልሚ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች እና አቅራቢዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና አዘጋጆችና አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዝናቡ አባመጫ እንዳሉት እንደ ሀገር የቡና ተጠቃሚነት ደረጃ አነስተኛ ነው።
ቡናን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር በጣዕም የተለዩ የቡና ዝርያዎችን ይዘን የአመራረታችን ሥርዓት ልማዳዊ በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየተገኘ አይደለም ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው ማኅበሩ ቡና አምራች አካባቢዎች ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት መጀመሩን ገልጸዋል።
"በቴክኖሎጂ የታገዘ የቡና አመራረት ሥርዓትን ከተከተልን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት ባለፈ በቡና ምርት በዓለም የተሻለ ደረጃ የማግኘት ዕድልን የሚያመጣ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጇብ በበኩላቸው በክልሉ ከ583 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ማሳ መኖሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ማሳ በዓመት ከ230 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ቢለቀመም በቡና ጥራት ችግርና ሌሎች ምክንያቶች ከ64 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
በቡና ግብይት፣ ጥራትና ዓለም አቀፍ የቡና ሕጎች ላይ በቂ ግንዛቤ ለመያዝና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ ምክክር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ 372 አልሚ ባለሀብቶችና 374 የቡና ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ለአልሚ ባለሀብቶች በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ በልማቱ ላይ አዎንታዊ ውጤት ለማምጣት እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው በአካባቢው የቡና ልማት ለማስፋፋት በተሰራው ሥራ የመጣው ውጤት በጥራት እንዲደገም መረባረብ ይገባል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዞኑ ከ27 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸው፣ በቀጣይ የቡና ጥራት አጠባበቅ ላይ ከአርሶ አደሮች፣ አልሚ ባለሀብቶትና አቅራቢዎች ጋር በመናበብ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የዘርፉን ተጠቃሚነት ከአገር ጥቅም ጋር አያይዞ ማየት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ሀብታሙ፣ የቡና ቅምሻና ሰርቲፍኬሽን ማዕከል በዞኑ ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በሚዛን አማን ከተማ ለአንድ ቀን በተዘጋጀ የምክክር መድረክ የቡና ምርትና ምርታማነት፣ ጥራትና የግብይት ሥርዓት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።