የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መተሳሰብ እና መረዳዳትን ያጎለበትንበትና የህሊና እርካታ ያገኘንበት ነው - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መተሳሰብ እና መረዳዳትን ያጎለበትንበትና የህሊና እርካታ ያገኘንበት ነው - ወጣቶች
ሐረር፤ ሐምሌ 08/2016 (ኢዜአ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር መተሳሰብ እና መረዳዳትን ያጎለበትንበትና የህሊና እርካታ ያገኘንበት ነው ሲሉ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተናገሩ።
በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በመዟዟር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወኑ ያሉ የወጣት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኞች ቡድን በሐረሪ ክልል በመገኘት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናውነዋል።
በዚህ አገር አቀፍ በሆነው ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች በሚሳተፉበት ወሰን የለሽ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ላይ ከተሣተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት ድግሪ ሃይለማርያም ይገኝበታል።
ወጣቱ እንዳለው በጎ ፈቃደኝነት በቋንቋና ብሔር የሚገደብ ሳይሆን በራስ ተነሳሽነት የሚሰራና የሂሊና እርካታ የሚያስገኝ ተግባር ነው።
ሁሉም ወጣቶች የህሊና እርካታ በሚሰጠው የበጎ ፈቃድ ተግባር ስራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል ሲልም ተናግሯል።
በጎነት ለራስ ስንቅ ነው፤ በዚህ በበጎ አድራጎት ተግባር በመሣተፌ ደስታ ተሰምቶኛል ያለችው ደግሞ ወጣት ሁሉአገርሽ ሙሉቀን ናት።
በክረምትም ሆነ በበጋ አቅመ ደካሞችንና ህጻናትን መደገፍ፣ በአገር ልማት ላይ የእራስህን አስተዋጽዎ ማበርከት ከአንድ ወጣት የሚጠበቅ ተግባር ነው ብላለች ወጣቷ።
ይህን ተግባር ወጣቱ ማጠናከር ይጠበቅበታል የሚል መልዕክት በማከል።
በጎ ፈቃደኝነት ማለት ካለህ ነገር ላይ ቀንሰህ ለአቅመ ደካሞች እና ትናንት ለእኛ ለደከሙ አባትና እናቶች መድረስ እና ማካፈል ነው ያለችው ወጣት ሐናን አህመድ ደግሞ፤ በዚህ ተግባር መሳተፌ የህሊናና የመንፈስ እርካታ አግኝቼበታለሁ ብላለች።
ወሰን ተሻግረን አገርንና ዜጎችን እየጠቀምን እንገኛለው ያለችው ወጣት ሀናን፤ ሌሎች ወጣቶችም በክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፋለች።
በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሙና አህመድ እንደተናገሩት በጎ ፈቃደኞቹ በየክልሉ በጎ ተግባራት በማከናወን ላይ ናቸው።
ከእነዚህ ተግባራት ጎን ለጎን የየክልሉን ባህል፣ ወግ እና እሴቶችን እንዲያውቁ ከማድረጉ በተጨማሪ ወጣቶች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲዳብር እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የወጣቶች ሰብዕናን ከመቅረጽ አኳያም ዝቅ ብለው ለአገራቸውና ለወገናቸው እንዲያገለግሉ፣ የስራ ባህልን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉ ባለፈ የሀገሪቱን ህዝብ አብሮነትና አንድነት አጠናክሯል ሲሉም ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ረምዚያ አብዱልዋሃብ በክልሉ 46ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉበት የሚገኝ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ወጣቶቹ የሚያከናውኑት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች 103ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በሐረሪ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን ቀጣይ ጉዟቸው ወደ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሆነም ተገልጿል።