በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዳማ፤ ሐምሌ 8/2016(ኢዜአ)፦ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ጠየቁ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ 'የአሽከርካሪዎች ድምፅ በጎ አድራጎት' የተሰኘ ማህበር በ75 ሚሊዮን ብር በሞጆ ከተማ ለሚያስገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ማህበራት የጭነትና የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በማህበራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
መንግስት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመንና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የወጪና ገቢ ዕቃዎችን ጨምሮ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲገባና ለመስኖ፣ ለበልግና ለመኸር እርሻ እንዲደርስ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎንም አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
''ትምህርት ቤት ትውልድ በዕውቀት፣ ስነ-ምግባርና ክህሎት የሚቀረፅበት ነው'' ያሉት ዶክተር ዓለሙ ዛሬ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ትምሀርት ቤትም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ በተቀመጠለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረው ሌሎች ማህበራት የማህበሩን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
የሞጆ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛሊ ሀሹ በበኩላቸው መስተዳድሩ ከተማዋ ጥራት ያላቸውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችን እያስገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፤ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በዚህም ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉት ላይ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በተለይ የኢንቨስትመንት ተቋማት በቂ የኃይል፣ የውሃ አቅርቦት፣ የመንገድና የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ትምህርት ቤትም በ1 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ የሚያርፍ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ በማድረጉ ረገድ ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር እንደሆነም አክለዋል።
'የኢትዮጵያ አሽከርካሪዎች ድምፅ በጎ አድራጎት ማህበር' ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሌ ሽፈራው፣ ማህበሩ የገቢና የወጪ እቃዎችን ከማጓጓዝና የጭነት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።
አሽከርካሪዎች በሙያቸው ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ትውልድ በዕውቀት እንዲቀረፅ በማሰብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትን ትምህርት ቤት በተቀመጠው ጊዜ ገንብተው ለማስረከብ ቃል ገብተዋል።