በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሠራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሠራት አለበት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅም ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የዝግጅት ሥራዎች መሠራት እንዳለበት ተገለጸ።
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) የሥርዓተ-ጾታና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ቢትረስ ማፔንጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አህጉሪቱን በንግድ ለማስተሳሰር ትልቅ ፋይዳ አለው።
በተለይም ለሴቶችና ወጣቶች በንግድ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ እድሎች እንዳሉት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ሌሎች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች እሴት ያልተጨመረባቸው በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ መጠቀም እንዳልቻሉ አስታውሰዋል።
እንዲያም ሆኖ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ምርቶች ላይ እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ስለሚያበረታታ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለመላክ አምራች የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶችና ወጣቶችን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን በዚህ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሀገራት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ለማምጣት የሚሰራው ኮሜሳም በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎችን መደገፍና ሀገራትን ለማበረታታት የተለያዩ መርኃ ግብሮችን እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም በአነስተኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፤ በተለይም ወደ መደበኛና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ የመደገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ይህም ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና መሳለጥ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥና ሌሎች ከቀረጥ ውጭ ያሉ ተግዳሮቶችን በሂደት በመቀነስ የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመ የንግድ ቀጣና ነው።
አሁን ላይ ከ15 በመቶ በታች የሆነውን የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ልውውጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2040 ከ15 እስከ 25 በመቶ እንደሚያሳድገው የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን(ኢሲኤ) መረጃ ያሳያል።