የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራርና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራርና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 8/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ደን ልማት አመራርና ሠራተኞች በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኩዪዋታ ተፋሰስ ላይ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ ።
አመራርና ሠራተኞቹ የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት በከተማ አስተዳደሩ ቱሎ ቀበሌ ኩዪዋታ ተፋሰስ ላይ በሚገኝ ከፍታ ስፍራ ላይ ነው።
በተከላው መርሃ ግብር ሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸው ተመላክቷል።
የወይራ፣ የቆላ ቀርከሃ እና ሌሎች ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የሀዋሳ ሐይቅንና የከተማዋን የተፈጥሮ ሥነ ምህዳር ለመጠበቅና የተጎዱ ቦታዎችን ለማከም የሚረዱ መሆናቸው ተጠቅሷል።
አመራርና ሠራተኞቹ ከችግኝ ተከላው ባሻገር ለ100 ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስና የጽሕፈት መሳሪያ ድጋፍ ለከተማ አስተዳደሩ አስረክበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የሲዳማ ክልል ደን፣ አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽታዬ ዩሙራ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ እና ሌሎች የአመራር አባላትና ሰራተኞች ተገኝተዋል።