ቀጥታ፡

የኢዜአ አመራሮች እና ሰራተኞች በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር በመገኘት ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራሮች እና ሰራተኞች በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር በመገኘት ማዕድ አጋሩ።

በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ፤ ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት የበርካታ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መጠለያ የሆነው መቄዶንያ በሚሰጠው መጠነ ሰፊ አገልግሎት ብዙ ቁም ነገር የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በማዕከሉ ውሰጥ የተጠለሉ አይነተ ብዙ ችግሮች የነበረባቸው ዜጎች በተደረገላችው እንክብካቤ ወደ ጤናማነት እንዲመለሱ መደረጉንም በተግባር መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

ከ7 ሺህ 500 በላይ ዜጎችን ተቀብሎ መንከባከብና ማስተዳደር ትልቅ መሰጠት እና ፅናት እንደሚጠይቅ ገልፀው፣ የማህበሩን መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ እና አጋር በጎ አድራጊዎችን አድንቀዋል።

መቄዶንያ እርስ በእርስ በመደጋገፍ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ከተረጂነት መውጣት እንደሚቻል ትምህርት የሚወሰድበት የበጎ ተግባር ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም ኢዜአ በቀጣይ መቄዶንያን በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በሙያ በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

መቄዶንያ አገልገሎቱንና ተደራሽነቱን ለማስፋት የጀመራችው ጥረቶች እንዲሳኩ ኢዜአ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን በሙያዊ አስተዋጽኦ በመደገፍ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ፤ ኢዜአ ለመቄዶንያ የሚዲያ ሽፋንና የማስታወወቂያ ስራ በመስራት ባለውለታ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች በዛሬው እለት ላደረጉት ጉብኝትና የማዕድ ማዕጋራትም አመስግነዋል።

መቄዶንያ ምንም ገቢ ማመንጫ ሳይኖረው በለጋስ ዕጅና ቅን ልቦች ድጋፍ የበርካቶች ሕይወት እንዲስተካከል፣ ከሕመም እንዲፈወሱ እና ከጉዳት እንዲያገግሙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በ27 ከተሞች ከ7 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎትና ክብራቸው ተጠብቆ እየተረዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቢኒያም፤ ስፍራው በትንሽ ስጦታ ብዙ በረከት የሚገኝበት በመሆኑ ሁሉም ይጎብኘን ሲሉ ጠይቀዋል።

'ኢዜአ በመቄዶንያ' በሚል መቄዶኒያን በየዓመቱ ሀምሌ ሰባት የመጎብኘት ቀን ለማድረግም ቃል ተገብቷል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም