ቀጥታ፡

የጎርጎራ ፕሮጀክት ታሪክ፣ ተፈጥሮና የሰው ልጅ ሀሳብ የተስማሙበት ድንቅ ስራ ነው - አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ የጎርጎራ ፕሮጀክት ታሪክ፣ ተፈጥሮና የሰው ልጅ ሀሳብ የተስማሙበት ድንቅ ስራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቆ በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ሁነት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ጎርጎራ እጅን በአፍ የሚያስጭን ድንቅ ፕሮጀክት ሆኖ መጠናቀቁንና ፊደል ሆኖ ታሪክ መጻፉን ገልጸዋል።

በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ የጎርጎራ ፕሮጀክት ታሪክና ተፈጥሮ በጉልህ የሚመሰክሩለት ድንቅ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ታሪክን አስቦ ከዛሬ ጋር በማስተሳሰር ውብ አድርጎ መስራትና ለቱሪስት መስህብ ማድረግ ይቻላል ብለው ያሳዩ የሀሳብና የተግባር ባለቤቶችን ማድነቅ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ይህ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።  

የጎርጎራ ፕሮጀክት ታሪክ፣ ተፈጥሮና የሰው ልጅ ሀሳብ የተስማሙበት ዘመን ተሻጋሪ ድንቅ ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ግዙፍ ሀሳብ አስቦ በተግባር መግለጥ ትልቅ እመርታ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ዋነኛ የቱሪት ማዕከል የሚሆን ድንቅ ስፍራ መሆኑን ጠቅሰው የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲጎበኙት ጋብዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም