የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክአ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ አስደናቂ ስፍራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክአ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ አስደናቂ ስፍራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክአ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ ከፍተኛ የቱሪዝም ሃብትና አስደናቂ ስፍራ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ተናገሩ።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቆ በትናንትናው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።
በምርቃት ስነ-ስርአቱ ላይ ከተገኙት ታዳሚዎች መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ በፕሮጀክቱ አሰራር ተደንቄያለሁ ብለዋል።
ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በሚያስደምምና በሚያስደንቅ ጥበብ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለኢኮቱሪዝም ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ከመልክአ ምድሩ ጋር ተሰናስሎ የሀገር ባህልንና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ የተገነባ አስደናቂ ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከግንባታው ጀምሮ በቀጣይም በአገልግሎቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደረግ መሆኑንም አድንቀዋል።
በቀጣይም የበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው የሀገር ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ጥሩ መሰረት የጣለ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት የአረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በዓለም የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በሚታይ ውጤት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና የሴቶች ማብቃት ዘርፍ ዳይሬክተር ኦሬሊያ ፓትሪዚያ ካላብሮ፤ የጎርጎራ ግራንድ ሪዞርት የተሰራበት ቦታና የመሬቱ አቀማመጥ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የጣና ሃይቅን ባማከለ ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥን መሰረት አድርጎ የተሰራ በመሆኑ የትኛውም ቱሪስት ሊጎበኘው የሚመኘው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥረትና ክትትል የተገነባ ዘመን ተሻጋሪ የሀገር ሃብት መሆኑንም ተናግረዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በተለይም ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ በማድረግና በማገዝ የዜጎችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
ከኬኒያ የመጡት አንድሪው ምቦጎሪ በበኩላቸው የጎርጎራ ግራንድ ሪዞርት ሁላችንም የምንኮራበት እጅግ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቱ በጣና ሃይቅ ተቃራኒ ያለው እይታ የሚማርክ፣ ባህል፣ ታሪክንና ዘመናዊነትን አጣምሮ የያዘ መጎብኘት ያለበት ድንቅ ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።