አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ የልማት ፕሮጀክቶችን እየተመለከቱ ነው

አዳማ  ፤ ሐምሌ 07/2016 (ኢዜአ)፡- የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በክልሉ አዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን በመከናወን ላይ ያሉትን የልማት ፕሮጀክቶች እየተመለከቱ ነው።

የሥራ ሃላፊዎቹ በተለይም በምሥራቅ ሸዋ ዞን እና በአዳማ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ስራ አጥነትን ለመቀነስ በመገንባት ላይ ያሉትን የልማት ፕሮጀክቶች ነው የተመለከቱት።

በአዳማ ከተማ አስተዳደር ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል የዶሮና የወተት ላሞች እርባታ፣ ለስጋ እንስሳት ማድለቢያና ለአሳማ እርባታ የተገነቡ ማዕከላት ይገኙበታል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ለከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በሰጡት ማብራሪያ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ስራ አጥነት ችግር ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው ብለዋል። 


 

በከተማው ለዶሮ፣ ለወተት ላሞች እርባታ፣ ለስጋ እንስሳት ማድለቢያና ለአሳማ እርባታ 1ሺህ 445 ማዕከላት በመንግሥትና በባለሀብቶች ተሳትፎ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን እንደ አብነት በማንሳት።

ለማዕከላቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት መሟላቱንም አክለዋል።

ከተገነቡት 1ሺህ 445 ማዕከላት ውስጥ 161ዱ በአስተዳደሩ ወጪ የተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማዕከላቱ ለዶሮና ለወተት ላሞች እርባታ ማዋላቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የእርሻ፣ የተቀናጀ አገልግሎትና ግንባታን ያካተተ የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተቋቁሞ በዘላቂነት የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባው በገለፃቸው አመልክተዋል።

የወተትና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም ጎን ለጎን  እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

800 የወተት ላሞች በቅርቡ ወደ ማዕከላቱ ይገባሉ ያሉት ከንቲባው፤ ይህም ለወጣቶች የሥራ እድል ከማስገኘት ባለፈ ለትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምግብ ጭምር ለማገዝ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም