እንቅስቃሴያችን የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት የሚያፀና ተግባር ነው - ወሰን ተሻጋሪ ወጣት በጎ ፈቃኞች - ኢዜአ አማርኛ
እንቅስቃሴያችን የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት የሚያፀና ተግባር ነው - ወሰን ተሻጋሪ ወጣት በጎ ፈቃኞች
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ መሳተፋቸው የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት በማፅናት የበጎ ፍቃድ ስራ እንዲያብብ እያገዘ መሆኑን ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ስራ ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።
ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የወሰን ተሻጋሪ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ዛሬ በድሬዳዋ ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል ሆነዋል።
ወጣቶቹ በድሬዳዋ ቆይታቸው ከችግኝ መትከል ባሻገር ወደ 10ሺህ ብር በማዋጣት ለአሸዋ የገበያ ማዕከል የእሳት አደጋ ተጎጂዎች ድጋፍ አድርገዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራ ተሳታፊ ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ጉልበት ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል እየተጉ ናቸው።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ኤርሚያስ ባህሩ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ስራ የእርስ በእርስ ትስስርን በማፅናት ችግሮችን በአንድነት ለመፍታት መረባረብን አስለምዷል ብሏል።
በየአካባቢው በምንጓዝበት ስፍራ ያሉትን ባህሎች፣ የአኗኗር ዘይቤዎችና ቋንቋዎች ለመረዳትና በቅርበት ለማወቅ አስችሎናል ያለችው ደግሞ ከአፋር ክልል የተሳተፈችው ወጣት ሉላ አህመድ ናት።
የተለያዩ ባህሎችና ማንነቶችን አውቄያለሁ፤የእኔንም አሳውቄያለሁ፤ እንደዚህ ተሳስረን የምንፈልገውን ሀገር እንገነባለን ስትልም ገልጻለች።
ከአወዳይ ከተማ የመጣው ወጣት ፋሚ አህመድ በበኩሉ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ስራ ወጣቱ ባለው ዕውቀትና ጉልበት ተባብሮ ሀገርን ከድህነት ለማውጣት እንደሚቻል ልምድና መሠረት እየሆነን ይገኛል ብሏል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ እንደተናገሩት፤ "በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከመላው ሀገሪቱ የተሰባሰቡ ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች ድሬዳዋ ተገኝተው በበጎ ተግባራት በመሰማራታቸው አስተዳደሩ ኩራትና ክብር ይሰማዋል።
ወጣቶቹ የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነትን አፅንተው በራስ አቅም እና ጉልበት ከተረጂነት ለመውጣት እንደሚቻል መንገድ ማሳየታቸውንም ገልፀዋል።
ወጣቶቹ ለእኛም አርአያ ሆነዋል፤ በክረምቱ ለጀመርናቸው የበጎ ስራዎች ትልቅ መነቃቃት ፈጥረዋል ሲሉም አክለዋል።
ወጣቶቹ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ደም በመለገስ፣ ችግኞች በመትከል፣ በግንዛቤ ትምህርት፣ በአካባቢ ፅዳትና ውበት ላይ በመሳተፍ አርአያነታቸውን እያሳዩ ናቸው ያሉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እንደገና ፍቃዱ ናቸው።
በድሬዳዋ ተገኝተው ችግኞች ከመትከል በዘለለ በአሸዋ ገበያ ስፍራ በደረሰው እሳት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ካላቸው ላይ 10ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።
ወጣቶች በቀጣዮቹ ቀናት በሐረር እና በጅግጅጋ ከተሞች ተገኝተው ተመሣሣይ የበጎ ፍቃድ ተግባራት እንደሚያከናውኑ ተመላክቷል።