ቀጥታ፡

በድሬዳዋ እና በክልሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቋል - የምክክር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ እና በክልሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

በሂደቱም እስካሁን የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ የተጀመረ ሲሆን በአዲስ አበባ የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ይታወቃል።

በቀጣይም በድሬዳዋ እና በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ገልጸዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰቢያ ላይ የተሳተፉ ዜጎች ለሀገር ይበጃል ያሉትን የመፍትሔ ሃሳብ በነፃነት በማቅረባቸው በሂደቱ ላይ ግልጸኝነት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሂደቱ ግልጸኝነት የተፈጠረበትና ህብረተሰቡንም ማስገንዘብ የተቻለበት እንደሆነ አስረድተዋል። 

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በድሬዳዋ እና በተለያዩ ክልሎች አጀንዳ ማሰባሰብ ጥናት በማካሄድ ቀጣይ የምክክር ምዕራፍ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።

በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች በምክክር የጋራ ሀገራዊ መፍትሔ ለመሻት እንዘጋጅ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክር ሂደቱ እስካሁን ህብረተሰቡ ላሳየው ድጋፍና በጎ አመለካከት ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም