የህብረተሰቡን ባህልና ስነ-ልቦና ታሳቢ ያላደረጉ የንግድ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይሰራጩ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የበለጠ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰቡን ባህልና ስነ-ልቦና ታሳቢ ያላደረጉ የንግድ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይሰራጩ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የበለጠ ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2016(ኢዜአ)፦ የህብረተሰቡን ባህልና ስነ-ልቦና ታሳቢ ያላደረጉ የንግድ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፉ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የበለጠ ሊጠናከር ይገባል ተባለ።
በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን በተደራጀ መልኩ መቆጣጠር የሚያስችል ደንብና መመሪያ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
አንዳንድ የንግድ ማስታወቂያዎች የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ከእውነታው ውጪ ተጋነው በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፉ ይስተዋላል።
የምግብና መጠጥን ጨምሮ የንፅህና መጠበቂያ ፣የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የግንባታ ግብዓቶችና ሌሎችም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች የህዝቡን ባህልና ስነ-ልቦና ታሳቢ እንዲያደርጉ የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ያስገድዳል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማስታወቂያ ክትትል ዴስክ ሃላፊ ዮናስ ፋንታዬ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የንግድ ማስታወቂያዎች ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጠ ይዘት እንዳይኖራቸው የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ያስገድዳል።
ባለስልጣኑ ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን የማያበረታቱና ከህብረተሰቡ ባህልና ስነ-ልቦና ውጪ የሆኑ የማስታወቂያ ስራዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፉ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ባለስልጣኑ ይህን ለመቆጣጠር ብቻውን የሚሰራው ስራ አለመኖሩን ጠቅሰው፣ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ ወደ ስራ መግባቱንም አብራርተዋል።
ለአብነትም ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፣ከትምህርትና ስልጠና ተቋም፣እንዲሁም ከኢትዮጰያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንን አመልክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ማስታወቂያዎችን ከከፍተኛ ትምህርት ስልጠና ተቋም፣ የአክሲዮን ጉዳዮችን ከካፒታል ማርኬት ባለስልጣን የምርትና አገልግሎት ደረጃዎችን ከተቆጣጣሪ አካላትና ከባለሃብቶች ጋር በመሆን የሚሰራጩ ማስታወቂያዎች ህግና ስርዓትን እንዲጠብቁ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የምግብ ምዝገባና ፍቃድ ባለሙያ በቀለች ጃቢሳ በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፋ የምግብና መጠጥ ማስታወቂያዎች ህብረተሰቡ ላይ ስነ-ልቦናዊ ጫና እንዳያሳድሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
ባለስልጣኑ ማንኛውም አይነት ምግብና መጠጥ ጥራትና ደህንነታቸው ተጠብቆ ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ ከምርት ሂደቱ ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ምርቱ የጥራት ደረጃውን አሟልቶ በባለስልጣኑ ከተመዘገበ በኋላ ማስታወቂያ እንዲነገርለት ፍቃድ ይሰጠዋል ብለዋል።
ባለስልጣኑ በተለይም ምርቶች ጥራትና ደህንነታቸውን ጠብቀው ለገበያ እንዲቀርቡና ከዚያ በኋላም ሂደቱን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በማንሳት።
የማህበራዊ ትስስር ገፆች መስፋፋትን ተከትሎ የተለያዩ ህገ-ወጥ ማስታወቂያዎች እንደሚሰራጩም ባለሙያዋ ያነሳሉ።
ይህን በተደራጀ መልኩ ለመከላከል ባለስልጣኑ ደንብና መመሪያ ማዘጋጀቱንም አመልክተዋል።