ጥንታዊቷ ጎርጎራ "በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት በስሟና በታሪኳ ልክ የሚመጥናትን ገፀ በረከት አግኝታለች-አቶ ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ጥንታዊቷ ጎርጎራ "በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት በስሟና በታሪኳ ልክ የሚመጥናትን ገፀ በረከት አግኝታለች-አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ ጥንታዊቷ ጎርጎራ "በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት በስሟና በታሪኳ ልክ የሚመጥናትን ገፀ በረከት አግኝታለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ዓይን የማያስከድን የድንቅ ውበት ባለቤት የሆነውን የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን ዛሬ መርቀናል ሲሉ አስፍረዋል፡፡
ጎርጎራ ቅኔ ነው፤ ጎርጎራ የልዕልና ምልክት ነው፤ ጎርጎራ የመቻል ምሳሌ ነው፤ ጎርጎራ ትናንትን ከዛሬ እና ነገን ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው ፣ ጎርጎራ የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የጎርጎራ ልማት ለጣና ተጨማሪ ሞገስ፣ ለጎንደር እና ባሕር ዳር ክብር፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ የመቻል ማሳያዋ ነው ያሉት አቶ ተመስገን የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት እንደ ሀገር በፈተናዎች የመፅናት አቅማችን የተገለጠበት ውጤታችን ነው ብለዋል፡፡
ጎርጎራ ንፅፅር የማይሻ፣ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ የተገነባ፣ ውበትን በልዩ ጥበብ የታደለና ሳይደበዝዝ ለትውልድ የሚተላለፍ ድንቅ የዕጅ ስራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ይህን ግሩም የቱሪስት መስህብ ለመገንባት ያቀዱ፣ ተከታትለውና መርተው ላስጨረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ንድፉን ለጣሉ ዕጆች፣ ለገነቡ ብርቱ ክንዶች እንዲሁም ውበትን ላላበሱ ዕሳቤዎች ምስጋናና ክብር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።