የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል የበኩላችንን እንወጣለን- የዘርፉ ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል የበኩላችንን እንወጣለን- የዘርፉ ተመራቂዎች
ሶዶ/ ሆስዕና ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሰለጠኑበት የዘርፉ ሙያ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የወላይታ ሶዶ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ተመራቂዎች ገለጹ።
ኮሌጁ ለ21ኛ ዙር በተለያየ መስክ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 135 ተማሪዎችን፤ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በግልገል ግቤ ቁጥር 3 በ"ፓወር ስትሪም" ያስተማራቸው 32 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቀዋል።
በወላይታ ሶዶ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ሰልጥኖ 3 ነጥብ 9 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ይስሐቅ ታምራት በሰጠው አስተያየት በሰለጠነበት የሰብል ልማት መስክ ዘርፉን ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናገሯል።
በአገሪቱ የግብርናው ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሶ፤ እድሉን በመጠቀምና የቀሰመውን ክህሎት በመተግበር ዘርፉን ለማሻሻል እንደሚተጋ ገልጿል።
በቆይታዬ በቀሰምኩት የተግባርና ንድፈ ሀሳብ ክህሎት አርሶ አደሩን በማማከርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋት ረገድ የድርሻዬን እወጣለሁ ያለችው ደግሞ የመስኖና ፍሳሽ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ባምላክ ግርማ ናት።
የእርሻ ልማት ስራ ባለው ውስን መሬትና ጉልበት መስራት እንደሚቻል ገልፃ፤ ለሽቅብ እርሻና ለመደብ ተስማሚ የእህል ዘር በመለየት በመስኖ እርሻ ማልማት እንደሚቻል አስረድታለች።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትምህርት ክፍል ተመራቂ በሀይሉ ከበደ ፤ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በጎርፍና ናዳ ምክንያት መሬት እንደሚራቆት ተናግሯል።
በሰለጠነበት ሙያ አካባቢው ተፈጥሮውን ጠብቆ እንዲቆይ ለማስቻል የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።
የኮሌጁ ዲን አሉላ ታፈሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሌጁ የአካባቢውንና አገሪቱን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኮሌጁ ለአከባቢው ማህበረሰብ በእንስሳትና ዓሳ እንዲሁም በአትክልት ልማት ስራ ሰርቶ ማሳያ በማዘጋጀት ልምድ እንዲቀስሙ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎች በመስራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ምሩቃን በቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ማህበረሰቡ ሲገቡ በተግባር በመለወጥ በአገሪቱ የግብርና ልማት ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነርና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋንታ ጋምአ ፤ ኮሌጁ ለግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኙ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል ።
በተለይም ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ በሰርቶ ማሳያ የሚያካሂዳቸው ተግባራት ዘመናዊ የግብርና አሰራርን ለማስረጽና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል ።
ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፣ የወላይታ ዞን አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና የኮሌጁ ቦርድ አባላት ተገኝተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በግልገል ግቤ ቁጥር 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በኤሌክትሪክና ኮምፒውተር ምህንድስና መስክ በ"ፓወር ስትሪም " ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 32 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሀብታሙ አበበ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምሩቃን ያገኙትን እዉቀት በመጠቀም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለልና ና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚጠበቅበትን ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝና ለዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘርፉ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ማስመረቁን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሩ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በእውቀትና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይልን በማደራጀት ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኤልክትሪካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂው ሄኖክ ተካልኝ ፤በተማረበት ሙያ በቀጣይ ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
በተመረቀችበት የትምህርት መስክ አመርቂ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ መሆኗ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀሟ እንደሆነ የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ ብርቱካን አቢ ናት።